የኤስዋ ቦርድ ሪፖርት በዶ/ር ዜና ብርሃኑ (የቦርድአባል) ለጠቅላላ ጉባኤ የቀረበ

Dr Zenaየተከበሩ የኤስዋ ጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢ

የተከበራችሁ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት

የተከበራችሁ የቦርድአባላት

ክቡራንና  ክቡራት

ከሁሉ አስቀድሜ የማኅበራችን መተዳደሪያ ደንብ በሚፈቅደውና ጠቅላላ ጉባኤው በሰጠን ኅላፊነት መሠረት ይህን በ 2020 (እ.ኤ.አ) የተከናወኑ ተግባራትን የሚገልፅ አጭር ሪፖርት ማቅረብ በመቻሌ ምስጋናዬን በቦርድ አባላትና በራሴ ስማ መግለጽ እወዳለሁ፡፡

ቦርዱ ቀደም ሲል በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ በተመረጡ 7 (2 ሴቶች እና 5 ወንዶች) አመራር አባላት አማካይነት ከማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ጋር በመሆን በማኅበራችን መተዳደሪያ ደንብ በግልፅ የተመለከቱትንና የሚከተሉትን ተግባራት ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

 • የማኅበሩን የዕለት ተዕለት ሥራ መከታተል
 • የሙያ ማኅበሩን ዳይሬክተርመሾም፤አፈጻጸሙን መከታተል፤መገምገም
 • በጠቅላላ ጉባኤ የተሰጡ ውሳኔዎችንና እቅዶችን በዳይሬክተሩ በኩል ተግባራዊ መደረጋቸውን መቆጣጠር፤መከታተል፤
 • የሙያ ማኅበሩን ፖሊሲ ደንብና መመሪያ ማውጣት፡ ማሻሻልና እንዳስፈላጊነቱም ለውሳኔ ለጠቅላላ ጉባኤው ማቅረብ፤
 • የማኅበሩን ዓላማዎች ለማስፈፀም የሚረዱ የገቢ ምንጮችን የገንዘብ ወይም የቁሳቁስ ድጋፍ የሚገኝበትን ዘዴ ማመላከት
 • የሙያ ማኅበሩን የሩብ ዓመትና ዓመታዊ የሥራ አፈፃፀም ሪፖርቶችና በጀት መርምሮ ማጽደቅ እንደ አስፈላጊነቱም ለጠቅላላ ጉባኤ ማቅረብ፤
 • በማኅበሩ የሚከፈቱ/የተከፈቱ የባንክ ሂሳብ ፈራሚዎችን እንደአስፈላጊነቱ ከማኅበሩ ሠራተኞች ውስጥ መመደብ/መተካት፡፡

በዚሁ መሠረት ቦርዱ በተጠቀሰው ዓመት ባካሄደው አራት መደበኛና ሁለት አስቸኳይ ስብሰባዎች ለማኅበሩ ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎችን ያሳለፈ ሲሆን ማኅበሩም የዕለት ተዕለት ሥራውን በተገቢው መንገድ እንዲያካሂድ የሚረዱ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡ ለተፈፃሚነታቸውም የቅርብ ድጋፍና ክትትል አድርጓል፡፡

በተካሄዱት መደበኛ ስብሰባዎች ላይ በማኅበራችን ውስጥ የተካሄዱ አጠቃላይ እንቅስቃሴዎችንና ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን በሚመለከት ከማህበሩ ዳይሬክተር መግለጫዎች ተደመጠዋል (ለምሳሌ-የሠራተኞች ቅጥርና ስንብት፡ የፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ወይም መስፋፋት)፡፡  እንዲሁም የየሩብ ዓመቱ የፕሮጀክትና የበጀት አፈፃፀም ሪፖርቶች በጽ/ቤቱ ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

መደበኛ ባልሆኑት ስብሰባዎች ደግሞ አራት ወሳኝ አጀንዳዎች ቀርበውና ተገቢው ውይይት ተደርጎባቸው እንዲፀድቁ ተደርጓል፡፡ እነዚህም 1ኛ.የ16ኛው ዓመታዊ ኮንፈረንስ የትኩረትና የመወያያ ነጥብን (Thematic area) መምረጥ እና የዚህ ጠቅላላ ጉባኤ አጀንዳዎችን መቅረፅ 2ኛ.ጽ/ቤቱ የውጭ ምንዛሪ አካውንት እንዲኖረው ማድረግ 3ኛ.በኤስዋና በዩኒሴፍ ትብብር የተዘጋጀውን የማኅበራችንን የህፃናት ደኅንነት ጥበቃ ፖሊሲን መርምሮ ማፅደቅ እንዲሁም 4ኛ.በአዲሱ የሲቪል ማኅበራት አዋጅ መሠረት እንደገና ተሻሽሎ የተዘጋጀውን የማኅበራችንን መተዳደሪያ ደንብ መርምሮ ለዚህ ጠቅላላ ጉባሄ የመጨረሻ ውሳኔ ማቅረብ ናቸው፡፡

Dr Zena 1የዛሬው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ የተጠራባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች በዕለቱ የጉባኤ ፕሮግራም/ መርሐ-ግብር ላይ በተገለፀው መሠረት በሚከተሉት አራት ነጥቦች ላይ ያተኩራል፡፡

 • የማኅበሩን ዓመታዊ ኦዲት ሪፖርት ማዳመጥና ማፅደቅ
 • የቦርዱን (ሊቀመንበር) ሪፖርት ማዳመጥና ተወያይቶ ማፅደቅ፡፡
 • የማኅበሩን ዓመታዊ የፕሮግራምና የበጀት አጠቃቀም ሪፖርትና የቀጣይ ዓመቱን ዕቅድ ማዳመጥና ማፅደቅ
 • የተሻሻለውን የማኅበሩን መተዳዳሪያ ደንብ እና መዋቅር ተወያይቶ ማፅደቅ እንዲሁም
 • ከቦርዱ አባላት መካከል 5ቱ ማለትም 1ኛ. አቶ ከበደ አየለ 2ኛ.ወ/ሮ ርብቃ ወልደሥላሴ 3ኛ.ዶ/ር አሉላ ፓንክረስት 4ኛ.ዶ/ር ዜና ብርሃኑ 5ኛ.አቶ ተሾመ መንግሥቴ የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን ዶ/ር ራሃዋ ሙሴና አቶ ሃዱሽ ሃለፎም የሥራ ጊዜአቸው አልተጠናቀቀም፡፡ በመሆኑም የዚህ ጠቅላላ ጉባኤ አንዱ ተግባር በ5ቱ የ ቦርድ አባላት ምትክ አዲስ የቦርድ አባላትን መርጦ መተካት ይሆናል፡፡

በመሆኑም በዛሬው  ዕለት የምናካሂደው የግማሽ ቀን የጠቅላላ ጉባኤ ስብሳባ ውጤታማ እንዲሆን ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋፅኦ እንድናደርግ አደራ እያልኩ ጉባኤው የተሳካና ፍሬያማ እንዲሆን ከልቤ እመኛለሁ፡፡

አመሰግናለሁ